የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግስ እና የዋዜማ አገልግሎት
ዜና ቤተክርስቲያን
በታላቁና በአንጋፋው በሚኒሶታ ደብረ ሰላም መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያ 3ኛው ዙር የመጀመሪያው ቀን መንፈሳዊ ጉባዔ ልዩ መንፈሳዊነት በያዘ መልኩ ትላንት በደብሩ ካህናቶች በጸሎት ተከፍቷል። ይህ ለ3 ተከታታይ ቀን የሚቆየው ጉባዔ ላይ ቤተክርስቲያን ካፈራቻቸው የወንጌል ሰባክያን መሀከል ለመናፍቃን በቂ መልስ በመስጠት የሚታወቀው መምህር ምሕረተአብ አሰፋ የወንጌል አገልግሎት ሰጥተዋል። መምህር ምሕረተአብ መቀመጫቸውን በሚኒሶታ ደብረ ሰላም መድኃኒዓለም በማድረግ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች በሲያትል፣ በዳላስ ፣ በአትላንታ፣ በዴንቨር ያደረጉት አገልግሎት በእግዚአብሔር ፈቃድ የተሳካ ሆኗል። በትላንትናው እለት በደብራችን የተጀመረው የሶስተኛውን ዙር ጉባዔ በመምህር ምሕረተአብ የስብከተ ወንጌል እና የዝማሬ አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን በዚህ ጉባዔ ላይ ተጋባዥ እንግዳ የሆኑት ወንድማችን ጥላሁን (ከዲሲ) ዝማሬውን በክራር በማጀብ ጉባዔውን ልዩ እንዲሆን አድርገውታል። በመጨረሻም ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ጸሎተ ምህላ ተደርጎ የትላንትናው መርሃ ግብር በጸሎት ተዘግቷል። ይህ ጉባዔ ቅዳሜና እሁድ የሚቀጥል ሲሆን በዚህ አጋጣሚ አገልግሎቱ ላይ ተገኝተሁ የበረከቱ ተካፋይ ይሆኑ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ጥሪዋን ታቀርባለች።
ክብር እና ምስጋና ለድንግል ማርያም ልጅ ለእርሱ ለሀያሉ አምላካችን ይሁን።
ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ
የማይቀርበት ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ በአናጋፋውና በታላቁ ደብር በሚኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መቀመጫውን ሚኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አድርጎ የሥብከተ ወንጌልን እሳት በዚህ ታላቅ ደብር ለኩሶ በምድረ አሜሪካ እያቀጣጠለ ያለው ታላቁ የተዋህዶ የወንጌል ገበሬ በመምህር ምህረተዓብ አሰፋ December 18, 19 and 20 ከ5 pm እስከ 8pm።
የቅዱስ ሚካኤል ንግስ በትላንትናው ዕለት በታላቅ ድምቀት ተከበረ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!
በትላንትናው ዕለት በደብራችን በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአምላክ ባለሟል የቅዱስ ሚካኤል በዓል ብፁዕ አቡነ አትናቲዎስ የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የድሬደዋና አካባቢዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ እንዲሁም ቤተክርስቲያን ካፈራቻቸው የወንጌል አርብኞች መካከል አንዱ መምህር ምሕረተአብ አሰፋ በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል። ከትላንት በስቲያ ከዋዜማ ፕሮግራም ጀምሮ ለሊት በማህሌት ከ2AM ጀምሮ በማህሌት፣ በቅዳሴ፣ በወንጌል ትምህርት፣ በኋላም ታቦቱ በብፁዐን አባቶች፣ በደብሩ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራን እና ከሩቅም ከቅርብም ከመጡ ምእመናን ጋር በመሆን በዝማሬና በእልልታ እየታጀበ ዑደት ካደረገ በኋላ በታላቁ አባት በአቡነ አትናቴዎስ ቃለ ምእዳንና ቡርኬ ተሰጥቶ ታቦቱ ወደመንበሩ ባማረ እና በደመቀ ሁኔታ ተመልሷል። ይህን በዓል ለየት የሚያደርገው የህዳር ሚካኤል ታቦተ ንግስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአውደ ምህረቱ ላይ ሆኖ ነበር የሚባርከው ነገር ግን ትላንት በእግዚአብሔር ቸርነት አየሩ ጥሩ ስለነበር ታቦቱ ወጥቶ ዑደት ተደርጓል። እግዚአብሔር አምላክ የከበረበት ጠላት ዲያቢሎስ ያፈረበት ሆኖ ተጠናቋል ክብር ለድንግል ማርያም ልጅ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር !
2ኛው ዙር ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ በመምህር ምሕረተአብ አሰፋ
ጥምቀት አይከለስም – የአቡነ አትናቴዎስ እና የአቡነ ዳንኤል መልዕክት
ዜና ደብረሰላም መድኃኔዓለም ዘሚኒሶታ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።
የሜኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም የ ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ቤተክርቲያን ዓመታዊውን የጥቅምት መድኃኔዓለም ክብረ በአል ብጹእ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎና በአማራ ክልል የኦሮሞ ሕብረተሰብ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብጹእ አቡነ ዳንኤል የድሬዳዋና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ታዋቂው ሰባኪ ወንጌል መምህር ምሕረተአብ አሰፋ በተገኙበት በትላንትናው እለት እጅግ በደመቀና ባመረ ሥነ ስርዓት ተከብሮ ውሏል።
በዚህ ቁጥሩ ከምንግዜውም በላይ ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ በተገኘበት በአለ ንግሥ ላይ ከዋዜማው ጀምሮ ሰፊ መንፈሳዊ አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን ብጹአን አባቶችም ለታዳሚው ሕዝብ ትምህርት፣ ቡራኬና ቃለ ምእዳን ሰጥተዋል።
ብጹእ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎና በአማራ ክልል የኦሮሞ ሕብረተሰብ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት አባታዊ ቃለ ምእዳን እና ቡራኬ የሜኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አንዳንዶች እንደሚናገሩት ከእናት ቤተክርስቲያን የተለ ሳይሆን ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ይህ ባይሆን ኖሮ እኛም የምንወዳቸውን እና የምናከብራቸውን ምእመናን መጥተን ባልባረክናችሁ ነበር ብለዋል። ብጹእነታቸው እንዳሉት እንደ አባቶቻችን ሕግና ሥርአት እምነት አንድ ነው ጥምቀትም አንድ ነው ምናልባት በእምነት የመሰነካከል ነገር እንኳን ቢኖር ለዚያም የተሰራ ሥርዐት አለ ከዛ ውጪ ግን አንድ ግዜ የተሰጠን ጥምቀት መከለስ አይቻልም፤ በጥምቀት ላይ ጥምቀት ቢፈጸም ግን እንደሻወር ነው የሚቆጠረው በማለት በብጹእ አቡነ ዘካርያስ እየተፈጸመ ያለውን ከሕገ ቤተክርስቲያን የወጣ ድርጊት የተሳሳተ መሆኑን አመልክተዋል።
ብጹእ አቡነ ዳንኤል የድሬዳዋና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው የእለቱን በአል የተመለከተ ትምህርት ከሰጡ በኃላ በተለይም ጥምቀትን አስመልክቶ በሰጡት ትምህርት ይልቁንም ሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያናት በጥንቃቄ የሚፈጸሙ እንደሆኑ አስረድተው ሚስጢረ ጥምቀትና ምስጢረ ክህነት ፈጽሞ የማይደገሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። ብጹእነታቸው እንዳሉት ጥምቀትን የሚደግም ማንም ቢኖር የቤተክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ እና አባቶች ፍጹም ርምጃ ይወስዳሉ ሲሉ አስገንዝበዋል። ይህ ክርስትና እንደገና የማንሳትን ተግባር እውነተኛ ኦርቶዶክስ የሆነና ህሊና ያለው ሰው በፍጹም የሚያደርገው ነገር አይደለም ካሉ በኋላ በሌላ ነገር መቀየም ይቻል ይሆናል ይህን ማድረግ ግን ከባድ ቅጣት የሥልጣነ ክህነት መያዝና ውግዘት እንደሚያስከትል አብራርተዋል።
ስለ ሜኒሶታ ደብረሰላም ቤተክርስቲያንም ሲመሰክሩ ይህች ቤተክርስቲያን በብዙ አንጋፋ ብጹአን አባቶች የተባረከች ስለሆነች ምንም አይነት ቅሬታ እና መጠራጠር እንዳይሰማችሁ እናረጋግጥላችኋለን ከዚህች ቤተክርስትያን ወዴትም እንዳትሔዱ እናሳስባችኋለን በማለት ምእመናንን የሚያጽናና እና የሚያንጽ ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ ወደዚህ ስንመጣ ምንም አይመስለንም ደስ እያለን ነው የምንመጣው፤ ከዚህ ከወጡት ልጆቻችን ጋርም ሰላምንም ለማምጣት ብዙ ጥረናል አሁንም እየጣርን ነው ብለዋል። ብጹእ አባታችንም /ብጹእ አቡነ አትናቴዎስ/ ብዙ ጥረዋል፤ ሰላም ለማምጣት ስልክ ደውለው ጆሯቸው ላይ ነው የዘጉባቸው ይህን ግፍ እግዚአብሔር እንዳይቆጥርባቸው እንጸልይላቸዋለን ብለዋል።
ቀደም ሲልም መምህር ምሕረታብ አሰፋ ሰፊ የሆነ የወንጌል ትምህርት የሰጡ ሲሆን በማስከተልም ቤተክርስቲያኑ ላለበት የተለያዩ ወጪዎች እና ወደፊት ለመስራት ላቀደው አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ግንባታ በእለቱ በተደረገ የገንዘብ ማሰባሰብ ዝግጅት 90ሺህ /ዘጠና ሺህ/ ዶላር ያህል ከምእመናን በጥሬ ገንዘብ በቼክና በቃል መግቢያ ቅጽ ተሰብስቧል።
ስላደረገልን ሁሉ እግዚአብሔር ይመስገን።
ዝማሬ በመምህር ምሕረተአብ አሰፋ
ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ በመምህር ምሕረተአብ አሰፋ
በሚኒያፖሊስ፣ ሴይንት ፖል እና አካባቢው ለምትኖሩ ምዕመናን በሙሉ
በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የድሬደዋና የአካበቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተገኝተው ቡራኬያቸውን ይሰጡናል ።
በኢትዮጵያ እና በመላው አለም በስባኪ ወንጌልነቱ ታላቅ ዝናና ያተረፈው ወንድማችን መምህር ምሕረተአብ አሰፋ ከፊታችን ኃሙስ ጀምሮ ታላቅ የወንጌል ዘር ሊዘራ ተዘጋጅቷል። ዕለቱም ጥቅምት 26 እና 27, 2008 ሐሙስ እና አርብ ከ400PM ጀምሮ (Nov 5 & 6) ሲሆን ቦታውም በMinnehaha Academy “3100 West River PKWY Minneapolis MN 55406″ ሚኒሶታም በወንጌል ስትናወጽ ታመሻለች – ወንጌል እንዳይሰበክ የሚቅበዘበዘው ዲያቢሎስም ድል ይመታል። ቅድስት እናታችን እመብርሃንም ከፈ ከፍ ትላለች። ታዲያ በዚህን ዕለት እንኳን መቅረት ማርፈድ ያስቆጫል።
ቦታ
Minnehaha Academy
3100 West River PKWY
Minneapolis MN 55406
ከሚኒያፖሊስ
Lake Streetን ይዘው ወደ ሴይንት ፖል ሲጓዙ 46ኛው ጐዳና ላይ ወደ ቀኝ ታጥፈሁ አስከ 32ኛው መንገድ ይሁዱ፤ Minnehaha Academyን 46 እና 32 ላይ ያገኙታል
ከሴይንት ፖል
Lake Streetን ይዘው ወደ ሚኒያፖሊስ ሲጓዙ 46ኛው ጐዳና ላይ ወደ ግራ ታጥፈሁ አስከ 32ኛው መንገድ ይሁዱ፤ Minnehaha Academyን 46 እና 32 ላይ ያገኙታል
ብፅዕ አቡነ አትናቴዎስ እና መምህር ምሕረተአብ አሰፋ ጉዞ ወደ ደብረሰላም መድኃኔዓለም
ብፅዕ አቡነ አትናቴዎስ እና መምህር ምሕረተአብ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሽኝት ሲደረግላቸው የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ
ታላቅ የምስራች“እግዚአብሔር ስለእናንተ ይዋጋል እናንተም ዝም ትላላችሁ።” ዘጸ.14፥14
ሁሉንም ነገር በጊዜው የሚያከናውን የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ሆኖ አባታችን ብጹእ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሊባርኩንና ቃለ ምእዳን ሊሰጡን ለሁለተኛ ጊዜ በደብራችን ይገኛሉ። እንዲሁም መምህር ምሕረተአብ አሰፋ በቤተክርስቲያናችን ለመጀመርያ ጊዜ ተገኝተው ሰፊ የወንጌል አገልግሎት ሊሰጡን ከብጹእ አባታችን ጋር ከቅድስት ሃገር ኢትዮጵያ ጉዟቸውን ጀምረዋል።እንደ እግዚአብሔር ፈቃድም ብጹእ አባታችን እና መምህር ምሕረተአብ ማክሰኞ ኦክቶበር 27/2015 ዓ.ም ከምሽቱ 6፡30PM ላይ በቤተክርስቲያናችን ደማቅ አቀባበል የሚደረግላቸው ስለሆነ ይህን መልእክት ያነበባችሁ የሚኒያፖሊስና አካባቢዋ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ሁላችሁም በደብረሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በመገኘት ከብጹእ አባታችን በረከትን እንድታገኙ ስንል ይህን አስደሳች ዜና በደስታ እናስተላልፋለን።የመጀመርያ ቀን የወንጌል ትምሕርት መርሐግብርም የፊታችን ሐሙስ ኦክቶበር 29/2015 ዓ.ም ከቀኑ 4፡30PM ጀምሮ በደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢ/ኦ/ተ/ቤ ክርስቲያን በመምህር ምሕረተአብ አሰፋ የሚሰጥ መሆኑን ከወዲሁ እናስውቃለን።“እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው።” ዘጸ 15፥ 3
የነሐሴ ኪዳነምሕረት ምስሎች – 2007 (August Kidanemheret Pictures – 2015)
የደመራ በዓል የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 15 (September 26) በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።
የአዲስ ዓመት ቅዳሴ – መስከረም ፩ ፳፻፰ (September 12, 2015)
ደብረ ታቦር በደብረሰላም
የኪዳነ ምህረት ንግስ ነሐሴ 16, 2007(August 22, 2015)
የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግስ – ሐምሌ 19, 2007
የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግስ እና የ5K ሩጫ/እርምጃ (St. Gebrael Celebration and 5K Run/Walk)
Saturday
7:30 – 11:30 5K Run/Walk
3:00PM – 6:00PM Eve
Sunday
Religious Hymn: 2AM – 7AM
Liturgy: 7AM – 10AM
Psalm, Sermon & Tabote Audet: 10AM – 12PM
በሰሞነ ህማማት ያውም በፀሎተ ኃሙስ ማውገዝ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮት የጣሰና ኢቂኖናዊ ነው ተባለ
የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳትሆን በከፍተኛ ደረጃ ኢትዮጵያዊነት የሚንጸባረቅባት የኃይማኖት ተቋም በመሆኗ፣ በዘር፣ በቋንቋ ፣ እንዲሁም በጐጥ ያልተከፋፈለች ስለነበረች በኃይማኖት ሽፋን ለረዥም አመታት አብሮ የኖረን ህዝብ በዕለተ ሆሳዕና ለምን ቀደሳችሁ ብሎ በካህናቱ ላይ በሰሞነ ህማማት ያውም በፀሎተ ኃሙስ በአባ ዘካሪያስ የተላለፈው ውግዘት የቤተክርስቲያንን አስተምህሮት የጣሰና ኢቂኖናዊ መሆኑን መልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ምህረት ዘውዴ ፍትሃ ነጋስትን በማጣቀስ እስተምረዋል። በመቀጠልም በሰሞነ ህማማት እንኳን ውግዘት ማውገዝ ይቅርና ይፍቱህ መባል እንኳን በተከለከለበት ጊዜ ያውም በፀሎተ ሀሙስ ለካህናቱ የውግዘት ደብዳቤ መስጠት የቤክርስቲያንን ህግ የጣሰ፣ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማይታወቅ፣ ወደፊትም የማይታይ መሆኑን ለተሰበሰበው ምዕመናን አስረድተዋል። የምስልና የድምጽ ዝርዝር መልዕክቱን ከቪዲዮው ይመልከቱ
በሰሞነ ህማማት የተላለፈው ውግዘት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ ነው ተባለ
የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትላንትናው ዕለት የቅዱስ ሚካኤልን በዓለ ንግስ ተጋባዥ እንግዳ መልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ምህረት ዘውዴ በተገኙበት በደመቀና ባማረ መልኩ ያከበረ ሲሆን፤ በዕለቱም በደብረ ሰላም ካህናት ላይ ለምን በዕለተ ሆሳዕና ቀደሳችሁ ፣ ለምን ህዝበ ክርስቲያኑን አሳልፋችሁ ለተኩላ አልሰጣችሁም በማለት በአባ ዘካርያስ የተላለፈው የሰሞነ ህማማት ውግዘት ኢቀኖናዊ መሆኑን አስተምረዋል።
መልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ምህረት ዘውዴ በመቀጠልም በሰሞነ ህማማት እንኳን ውግዘት ማውገዝ ይቅርና ይፍቱህ መባል እንኳን በተከለከለበት ጊዜ ያውም በፀሎተ ሀሙስ ለካህናቱ የውግዘት ደብዳቤ መስጠት የቤክርስቲያንን ህግ የጣሰ መሆኑን ለተሰበሰበው ምዕመናን አስረድተዋል። የምስልና የድምጽ እንዲሁም ዝርዝር ዘገባውን ይዘን እንመለሳለን።
የቤተ ክርስቲያኗ ምዕመናን የመልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ምህረት ዘውዴ ስብከት በዲቪዲ ተባዝቶ አንዲቀርብላቸው በጠየቁት መሰረት በትላንትናው ዕለት ማለትም እሁድ ነሐሴ 28 2007 ወይንም July 5, 2015 የመጀመሪያውን ዙር ያከፋፈልን ሲሆን በተከታታይ ሳምንታትም ሁሉም ምዕመን እስኪዳረስ ድረስ አቅርቦቱ የሚቀጥል መሆኑን በታላቅ አክብሮት እንገልፃለን።
የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን